የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በማስተዋወቅ በመሳብ ሥራ ባስመዘገበችው የላቀ ውጤት ሸለመ

bs2_0

ኢትዮጵያ ሽልማቱን ያገኘችው ትናንት ኅዳር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደው በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ዘጠነኛ የኢንቨስትመንትና ልማት ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የ2017 ሽልማትን ያገኘችው በትኩረታዊ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ እና ዘላቂነት ባለው ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት በየዓመቱ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ኢንቨስትመንት በመሳብ አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ አገሮች የሚሸልመው ሽልማት ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የሞሪሽየስ የኢንቨስትመንት ቦርድ እና የስፔኑ ኮፋይደስ የ2017 ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በሽልማት ስነስርዓቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ የኢንቨስትመንት ዳይሬክተር እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ለሽልማቱ ካበቋት መለኪያዎች መካከል መንግስት ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በተቀናጀ እና በተሳለጠ መልኩ በመሳብና ድጋፍ በመስጠት ባከናወነቻቸው ስራዎች ነው።

በተለይም የኢትዮጵያ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ባህርያት፣ የአረንጓዴ የኢንዱስትሪ የልማት ስትራቴጂ ለማሳካት ከብክለት ነፃ ተደርገው የተገነቡ እንደ ሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ታዋቂ ኢንቨስተሮች እንዲገቡ ያስቻለ ትኩረታዊ የኢንቨስተሮች አመራረጥና ኢንቨስተሮቹ የተደረገላቸው ድጋፎች የሚመሰገንና ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ቀጥተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ፥ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴዎችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን መቻሉን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ ብዙ ሰውን መቅጠር የሚያስችሉ ወይም ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ እንደ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ያሉት ዘርፎች በርካት ወጣቶችን ወደ ሥራ የሚያስገቡና ለሴቶች እኩል ዕድልን የሚሰጡ፣ ባጠቃላይ ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊና አካባቢያዊ ደረጃዎችን ትኩረት ሰጥቶ የመስራትና የማሟላት ሂደትና አገሪቱ ስትራቴጂክ አገልግሎቶችን ለማቅረብ፣ ጥራት ያለው ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳቧ፣ ለኢንቨስተሮች ተስማሚ የሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎችንና አሰራሮች ማድረጓ ይህንን ሽልማት እንድታገኝ አድርገዋታል ብሏል፡፡

በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ የተመራ የልዑካን ቡድን ሽልማቱን የተቀበለ ሲሆን፣ በሲውዘርላንድ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና በጄኔቫ የተመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር አቶ ነጋሽ ክብረት በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተግኝተዋል፡፡

በቅርቡም የዓለም ባንክ ውጤታማ የፓሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎችን በመተግበር ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሀገሪቱ በዓመቱ ባስመዘገበችው አመርቂ ውጤት የኮከብ ፈፃሚ ደረጃ (2017 Star Reformer Award) ለኢትዮጵያ መንግስት እንደተበረከተለት ይታወሳል። ይህም ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2025 በአፍሪካ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ማዕከል ለመሆን ያነገበችውን ራዕይ ለማሳካት፥ በትክክለኛ መስመር ላይ መሆኗን ተጨማሪ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡