በውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዜጎች ላይ ጫና እንዳያስከትል ዝግጅት መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ

545f059c81a6527a37d5560d26785bf0_XL
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዜጎች ላይ ጫናና የዋጋ ንረትን እንዳያስከትል መንግስት ዝግጅት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቅርቡ በብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ከተደረገው ማስተካከያ ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ ማሻሻያው የተደረገበትን ምክንያት ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ጀምሮ በተደረገው የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ዙሪያ የመንግስትን አቋሞች እና እርምጃዎች አቅርበዋል።
ባላፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱ ከአሁኑ ውጭ ለስድስት ጊዜ ያህል የብርን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻሏን አንስተው፥ የአሁኑ ማሻሻያ ሲደረግ መሰረት ያደረጋቸውን ነጥቦች ዘርዝርዋል።
አርሶ አደሮችም ሆኑ ሌሎች ባለሃብቶች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛት እንዲያመርቱ ለማበረታታት እና ባለፉት ዓመታት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ቢጨምሩም ምርቶች ከሚሸጡበት የገንዘብ ዋጋ አንጻር ብር ጠንካራ በመሆኑ በወጪ ንግዱ ላይ ጫና በመፍጠሩ ማሻሻያ መደረጉን ነው ያነሱት።
የማምረቻ ኢንዱስትሪው በአብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛት አምርቶ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ሲባል በዋናነት ማሻሻያው መደረጉን አንስተዋል።
ሆኖም የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን ለመከላከል መንግስት አስቀድሞ የተዘጋጀባቸውን ጉዳየችንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል።
በዚህም፦
ከምንዛሬ ተመን ማሻሻያው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የነዳጅ እና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት መንግስት የሚሰራ ሲሆን የነዳጅ  ጭማሪ ከተከሰተም መንግስት በድጎማ ለመሸፈን ወስኗል ብለዋል።
(ስንዴ፣ ዘይት እና ስኳርን) ጨምሮ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች እና ሸቀጦች የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት ስርጭት እና የዋጋ        ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ እና የውሃ ታሪፍ ጭማሪ አይደረግም ነው ያሉት።
ማሻሻያው ሀገሪቱ ለድርቅ ያልተጋለጠችበት እና ከፍተኛ የመኸር ሰብል ምርት በሚገኝበት ጊዜ እንዲደረግ መወሰኑ በገበያው ያለውን የምርት መጠን እንዳይጓደል እና የእህል ዋጋ ንረት እንዳይኖር ያደርገዋል ብለዋል።
ከምንዛሬ ተመን ማሻሻያው በፊት ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች    ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፥ እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።
ገበያውን ለማረጋጋት የተቋቋመው አለ በጅምላ መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ለ2 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይንም በማብራሪያቸው ተመልክተዋል።
የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና ተጠቃሚነት ከዓቢይ ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል ዋና ሆኖ በበጀት ዓመቱ እንደሚሰራበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ የወጣቶች ስትራቴጂ እና ፓኬጆች ተቀርፀው ወደ ስራ መገባቱን ነው ያነሱት።
ክልሎችም በጀት መድበው ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እና ዘርፈ ብዙ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በሀገሪቱ 6 ሚሊየን ስራ አጥ ወጣቶች እንደሚገኙ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ባለፈው ዓመት ለ2 ሚሊየን ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የወጣቶች የስብዕና እና የስነምግባር ግንባታ ትኩረት እንደሚሰጠውም ነው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ለዚህም በከተማ ወጣቶች እርስ በእርስ የሚማማሩባቸው ማዕከላት እንዲኖሩ እየተደረገ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቶችም በስነዜጋ እና ስነምግባር ትምህርት የተሻለ ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በገጠር የወጣቶች የትምህርት ትራንስፎርሜሽን ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የገጠር ግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ መንግስት የያዘውን አቅጣጫ እና በበጀት ዓመቱ ምን እንደሚሰራም በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ተብራርቷል።
ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮች እና በአርብቶ አደሮች የተመሰረተ የግብርና ልማትን ተግባራዊ እያደረገች ነው ብለዋል።
የሰብል ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ፣ በቂ የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና ሌሎችም ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዲደርሳቸው እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በአፍሪካ የመጀመሪያው ሊሆን የሚችል እያንዳንዱ አፈር የሚጠቀመውን የማዳበሪያ አይነት በምርምር የማረጋገጥ ስራ ተሰርቶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።
ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፥ ለዚህም በየክልሎች የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑን ነው ያነሱት።
ባለሃብቶችም ግብርናውን በማዘመን ረገድ ሚና ያላቸው ሲሆን፥ ወጣቶችም ዘመናዊ በሆነ ግብርና እንዲሳተፉ ይሰራል ነው ያሉት።
አርብቶ አደሮችም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የእንስሳት እርባታን እንዲያከናውኑ ከመደገፍ ባሻገር በሰብል ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል።
በአጠቃላይ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በውጪ ንግድ የላቀ ዋጋ የሚያስገኙ ስራዎችን እንዲያጠናክሩ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ግብርናው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሆኖ እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶታል።
ለዚህም ከግማሽ የሚልቀው የሀገሪቱ አርሶ አደር በመስኖ ልማት እንዲሰማራ መደረጉን ያነሱ ሲሆን፥ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።።
ከማምረቻ ዘርፍ አንፃር
የማምረቻው ዘርፍ ፈጣን እድገት እያስመዘገበ ሲሆን፥ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።
በክልሎች የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪ ፓርኮች እየተገነቡ ሲሆን፥ በከተሞች አካባቢም በርካታ የማምረቻ እንዱስትሪዎች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዘርፉ እድገት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን እንዲሳተፉ እየተደረገ ሲሆን፥ በተመረጠ ሁኔታ የውጭ ባለሃብቶች እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የኤሌከትሪክ ሃይል እና የንፁህ መጠጥ ውሃን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ሊሰራ ያቀዳቸውን ተግባራት አስቀምጠዋል።
በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባልተማከለ ሁኔታ በክልሎች እንዲሆን መወሰኑን ተናግረው፥ የሃይል ማመንጨት ስራዎች በፌደራል መንግስት የሚሰሩ ሲሆን በዋናነትም በታዳሽ ሃይል ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው ያብራሩት።
የንፁህ መጠጥ ውሃን በተመለከተ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ተደራሽ እየተደረገ ሲሆን፥ ትናንሽ እና ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲቀርብላቸው ይሰራል ብለዋል።
በአርብቶ አደር እና በቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የከርሰ ምድር ውሃን በጉድጓድ ቁፋሮ በማውጣት ለሰዎች እና ለእንስሳት በቂ ውሃ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያነሱት።
ታዳጊ ክልሎች ከሌሎቹ ተመጣጣኝ እድገት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ጠቁመዋል።
ለዚህም በክልሎቹ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ የሰው ሃይል እና የውሃ ክምችት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እና የግል ባለሃብቶችም በስፋት እንዲሰማሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
ከምግብ ዋስትና አኳያ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ያለው አካባቢ ድርቁን እንዲቋቋም እና የምግብ ዋስትናውም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ
የኢትዮጵያ እና የጎረቤት ሀገራት ግንኙነት እና ፋይዳውን በመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራርያ ሰጥተዋል።
ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት በተለይም ከሱዳን እና ከጂቡቲ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ ስራ መስራቷን አንስተዋል።
ለዚህም የሀገራቱን ወደብ መጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲጠናከሩ፥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በየብስ እና በባቡር ትራንስፖርት ጭምር እንዲጠናከር እየተደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን መነሻ ያደረገ የኤሌክትሪክ ሃይል ትስስር ለመፍጠር እየሰራች ነው ብለዋል።
በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ሰላም የማስፈን ስራዎች እንደጠናከሩ እና ስምምነቶችም ተግባራዊ እንዲሆኑ፥ ኢትዮጵያ የኢጋድ ሊቀመንበር እንደመሆኗ በርካታ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
ለአብነትም በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል የተቃዋሚ ወገኖችን ጭምር የሚያሳትፍ የሰላም ኮንፍረንስ ለማካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለፁት።
በሶማሊያ አልሸባብን ለመዋጋት እና በምርጫ የሚያስተዳድር መንግስት እንዲመጣ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ስራ ሰርታለች ብለዋል።
ለዚህም ከአሚሶም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጭ የሶማሊያ ሰላም ከሚያስገኘው ፋይዳ አንፃር ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ የመከላከያ ሰራዊቶቿን ወደ ሶማሊያ ማሰማራቷን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ ተዳክሞ የነበረው አል ሸባብ በቅርቡ በርካታ ዜጎች የሞቱበትን ጥቃት አድርሷል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም አልሸባብን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር እንደትምሰራ የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም፥ በሀገሪቱ የሚደረገው ምርጫ ሰላማዊ እና የህዝብ አመኔታ ያለው እንዲሆን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።