ሀላፊነት በጎደለው መልኩ በሚዘግቡ የሚዲያ አካላት ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል-ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም

pm parlama
በሀገሪቱ የተፈጠሩ ግጭቶችን ሀላፊነት በጎደለው መልኩ በሚዘግቡ የሚዲያ አካላት ላይ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡
ሚንስትሩ ባለፈው መስከረም 29 ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ያቀረቡትን ንግግር አስመልክቶ በቀረበው የድጋፍ ሞሽንና ከአባላቱ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በሀገሪቱ ያሉ ሚዲያዎች ግጭቶች ሲዘግቡ በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማያባብስ መልኩ በሃላፊነት መንፈስ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ይህንንም አሰራር በመጣስ ዘገባዎችን በሰሩና በሚሰሩ የሚዲያ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል፡፡
በሚዲያ አካላት የሚታዩ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ በሀገሪቱ የሚዲያ ስርዓቱን ለማሻሻል የሪፎርም ስራዎች ተጀምሯል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም፡፡
በዚህም በዘርፉ በክህሎትና በአመለካከት ያለውን ደካማ የሰው ሀይል አቅም ለማጎልበት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የተለያዮ ስልጠናዎች ለመስጠት በበጀት ዓመቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያዎችን በባለቤትነት የሚመሩ ኩባንያዎች በህዝብ መካከል ጥላቻንና ግጭቶችን የሚያባብሱ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር የገቡት ቃል እንዲተገብሩ ይሰራል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡