ኢትዮጵያ የዓለም ስራ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ አካል መደበኛ አባል ሆና ተመረጠች

19055872_442092746161683_7593213596463711708_o

 በጄኔቫ ከእ.ኤ.አ. ጁን 5-16/2017 ስር እየተካሄደ ባለው የዓለም የሥራ ኮንፈረንስ (International Labour Conference) የድርጅቱ አስተዳደር አካል (Governing Body) ለቀጣይ ለሶስት ዓመታት (እ.ኤ.አ 2017-2020) በመደበኛ እና ተለዋጭ አባልነት የሚያገለግሉ ሀገራት ምርጫ እ.ኤ.አ. ጁን 12 ቀን 2018 አካሂዷል፡፡ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ በተመራ እና የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን እና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አመራሮችን የያዘ የልዑካን ቡድን በተገኙበት በድርጅቱ መቀመጫ በጄኔቫ በተካሄደ ምርጫ ኢትዮጵያ የመደበኛ አባል ሆና ተመርጣለች፡፡ ኢትዮጵያ የመንግስታት፣ ሰራተኞች እና አሰሪዎች 252 ተወካዮች በተሳተፉበት ምርጫ 238 ድምጽ በማግኘት ተመርጣለች:: አባል ለመሆን 122 ድምጽ በሚጠይቀው በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ  ከአፍሪካ ከቀረቡ ሀገራት መካካል ከፍተኛውን ድምጽ አግኝታለች፡፡  ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሴቶ፣ ሞሪታንያ፣ ኮትዲቯር እና ሴኔጋል በመደበኛ አባልነት ተመርጠዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ውስጥ በተለዋጭ አባልነት እያገለገለች ያለችው ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ስራ አስፈጻሚ አካል መደበኛ አባል ሆና ለመጨረሻ ጊዜ ያገለገለችው ከእ.ኤ.አ 1999-2002 ነው፡፡

ኢትዮጵያ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሆና መመረጥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ለድህነት፣ ለወጣቶች ፍልሰት ምክንያት የሆነውን ሥራ አጥነትን እና በሥራ አካባቢ ያሉ የመብት መጓደሎችን በመቀነስ በ2030 በዘላቂ ልማት ግቦች የተቀመጠውን ምቹ ሥራ አጀንዳ (decent work and full and productive employments) ለማሳካት ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ኢትዮጵያም ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነትን በማጠናከር፣ በተለይ በወጣቶች ሥራ ፈጠራ መንግስት 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ የሚያስችል የቴክኒክ እና የፓሊሲ ድጋፍ ለማጎልበት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

ኢትዮጵያ ድርጅቱ ከተመሠረተ አራት ዓመታት በኋላ የተቀላቀለች ከመሆኑ አንጻር ድርጅ መቶኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ የሥራ አስፈጻሚ አካል አባል እና የአፍሪካ ቡድን አስተባባሪ ሆና መመረጧ ልዩ ትርጉም ያለው ሲሆን በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ እያደገ የመጣውን የሀገራችን ተሰሚነት ለማጠናከርም ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከጉልበት እና ወረት ዝውውር(labour and capital mobility)፣ ፈጣን ቴክኖሎጂ እድገት እና ዲጂታይዜሽን፣ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች መስፋፋት(global supply chains)ጋር ተያይዞ ምቹ ስራ(decent work) ለማረጋገጥ እየገጠመ ያለውን ፈተና በመገምገም በቀጣዩ ክፍለ ዘመን የድርጅቱን ራእይ ለማስቀመጥ ሰፊ ስራዎች እያከናወነ ባለበት ወቅት ሀገራችን አባል ድርጅቱ እደረገ ያለው ለውጥ  የሀገራችንን እና የአፍሪካን ጥቅም እና ፍላጎት ከግምት የሚያስጠብቅ እንዲሆን ለማድረግ ይረዳል፡፡

በመሆኑም ሀገራችን በተለይ ድርጅቱ በሚቀጥሉት ሶሰት ዓመታት መሠረታዊ ማህበራዊ ዋሰትና ማረጋገጥ (Social Protection) መሠረታዊ የሥራ መብቶች እና ጽንሰ ሀሳቦችን ተፈጻሚነት ለማሳደግ፣ በመንግስት፣ በሠራተኞች እና በአሠሪዎች መካከል ያለውን የሶስትዮሽ አሰራር መርሆዎች (tripartitism) በማጎልበት ማህበራዊ ምክርን(social dialogue)ማሳደግ እና ሥራ ፈጠራ እና ዘላቂ የቢዝነስ ልማት (sustainable  Enterprise Development) ለማጠናከር በሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ትንቀሳቀሳለች፡፡ በተጨማሪም አሰሪና ሰራተኛ አስተዳደር ስርዓትን በማጠናከር (Labour Administration and Inspection)፣ የሰራተኞች ፍልሰት (Labour migration) እና መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ (Informal Economy) ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ (formal Economy) ሽግግር ላይ ከድርጅቱ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ሰፊ ስራዎች ታከናውናለች፡፡

122 አባላት ያሉት የዓለም የሥራ ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ አካል ከእ.ኤ.አ. 1919 ጀምሮ በስራ ላይ ያለ ሲሆን ካሉት 56 መደበኛ አባላት አሉት፡፡ ከእነዚህም መካካል 28 አባላት መደበኛ አባላት የሚመረጡት ከመንግስታት ሲሆን ከሠራተኞች 14 እንዲሁም ከአሠሪዎች 11 አባላት ይኖሩታል፡፡ በተመሳሳይ ስራ አስፈጸሚው ካሉት 66 ተለዋጭ አባል ሀገራት መካከል 28 መንግስታት፣14 ሰራተኞች እና 14 አሰሪዎች አባላት ይኖራቸዋል፡፡የስራ አስፈጻሚው አካል የዳይሬክተር ጄኔራሉን ምርጫ ጨምሮ፣ የድርጅቱን ሥራ በተመለከተ አቅጣጫ የመስጠት፣ የድርጅቱን ፋይናንስ የመፍቀድ መቆጣጠርና እና  ተያያዥ ሌሎች ስልጣኖች አሉት፡፡

በዕለቱ ለ106ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት ኮንፈረንስ  የአየር ንብረት ለውጥ በስራ ላይ ላይ ያለውን ተጽዕኖ (climate change impact on the world of work) በተመለከተ በቀረበለት ሪፖርት ላይ ክቡር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ ንግግር አቅርበዋል፡፡ ሚኒስትሩ የአካባቢ ለውጥ በአፍሪካ ደሀ ገበሬዎችን ወደ ከፋ ድህነት እየገፋ መሆኑን ጠቅሰው የዓለም የሥራ ድርጅት አባል ሀገራት እና የሠራተኛ እና የአሠሪ ድርጅቶች የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ እንዲታገሉ አቅርበዋል፡፡ የዓለም ሥራ ድርጅት ሥራን አረንጓዴ ለማድረግ (Green Jobs initiative ) የጀመረውን ፕሮገራም በማድነቅ  ድርጅቱ ለአፍሪካ በቂ ትኩረት በመስጠት በተለይ በታዳሽ ኃይል ልማት የስራ እድሎች ፈጠራ እና ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የግብርና (Climate smart agriculture solutions) ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል፡፡ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚመጣ ድርቅ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመገንዘብ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመቅረጽ የካርቦን ልቀትን በ2025 ዜሮ ለማድረስ እየሰራች እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በሚደረገው ሽግግር ውስጥ ታዳሽ ኃይልን በማጎልበት፣ የደን ልማትን በማስፋፋት ተጨማሪ አረንጓዴ ስራ እድሎች በመፍጠር ረገድ እና ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አዃያ በትክክለኛ ገዳና ላይ ላይ መሆንዋን አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መነሻነት የዓለም ስራ ድርጅት በአረንጓዴ ስራዎች ላይ በሚያደርገው ፕሮጀክት ኢትዮጵየ በትብብር የምትሰራ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡