የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ወጥቷል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሞኑን የ40/60 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ወጥቷል በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ቤቶቹን ተረክቦ ለተጠቃሚዎች በዕጣ ለማስተላለፍ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የኢንተርፕራይዙ የኮሙኒኬሽን የስራ ሒደት መሪ አቶ ዮሐንስ አባይነህ እንደገለጹት፥ በሶስት ምዕራፎች በሚካሄደው የ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም 39 ሺህ ቤቶች እየተገነቡ ነው።

ከነዚህ መካከል የ1 ሺህ 292 ቤቶች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ከንግድ ባንክ ጋር ርክክብ ለመፈጸም የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ዕጣው ለእነማን እንደሚወጣ እስካሁን የተወሰነና በባንኩና በኢንተርፕራይዙ መካከልም የተደረገ ስምምነት የለም።

ነገር ግን በመመሪያው መሰረት ከከፍተኛው ቆጣቢ በመጀመር ወደ ዝቅተኛው በመውረድ እንደሚወጣ አመልክተው በጅምላ ወይም በጥቅል የሚኬድበት አሰራር አለመኖሩን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ቁጠባን መርህ ያደረገ በመሆኑም “እያንዳንዱ ቆጣቢ እርስ በእርሱ ተወዳድሮ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ቤቶቹን እንዲያገኝ ይደረጋል” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንሲዩመር ብድር አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኪዳኔ መንገሻ በበኩላቸው ባንኩ በቅርቡ ቤቶቹን ተረክቦ ለተጠቃሚዎች በዕጣ ለማስተላለፍ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት “ዕጣው ወጥቷል፣ ንግድ ባንክ በዕጣው የሚካተቱ ተመዝጋቢዎች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል” እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ቤቶቹን ለማግኝትና ዕጣ ውስጥ ለመካተት ቅድሚያ የቆጠበ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑንና ለዚህም ባንኩ አስቀድሞ ከቤት ፈላጊዎች ጋር ውለታ መግባቱን አስታውሰዋል።

በፕሮግራሙ165 ሺህ የሚደርሱ ቤት ፈላጊዎች የተመዘገቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 145 ሺህ የሚሆኑት ቁጠባቸውን በመክፈል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከል ደግሞ 14 ሺህ የሚሆኑት ክፍያውን መቶ በመቶ ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዙ ቤቶቹን ለባንኩ ካስረከበ በኋላ ቤት ያላቸውን ሰዎች የማጣራት ስራ እንደሚሰራ፣ በፍርድ ቤት ስም የለወጡና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችም እንደሚታዩ ተናግረዋል።

ዕጣው የሚወጣበትን ቀን ባንኩ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ተመዝጋቢዎች እስካሁን ባሳዩት ትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቀዋል።

ከ40/60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም ዕጣ የሚወጣባቸው በክራውንና ሰንጋተራ ሳይቶች የተጠናቀቁት 1 ሺህ 292 ቤቶች ናቸው።

ምንጭ፦ ኢዜአ